the green flood

the green flood

Thursday, April 3, 2008

ኢትዮጵያዊያን የማያውቃቸው ታላላቅ አትሌቶቻችን

ሃገራችን፡ታላቋ፡የሩጫ፡ሃገር፡የሚለውን፡ስም፡ለማግኘት፡የቻለችበት፡ምክንያት፡ለማንም፡ሰው፡ግልጽ፡ነው።ኢትዮጵያ፡ሃገራችን፡በተለያዩ፡ኢንተርናሽናል፡ውድድሮች፡መሳተፍ፡ከጀመረች፡ከግማሽ፡ምእተ፡ዓመት፡በላይ፡አስቆጥራለች።የኢትዮጵያ፡አትሌቶች፡ድልንም፡መጎናጸፍ፡የጀመሩት፡ከመጀመሪያ፡ተሳትፎ፡ማግስት፡ሲሆን፡ይህ፡ከሃምሳ፡ዓመታት፡በላይ፡የቆየውና፡ሲወራረስ፡የመጣው፡ጀግንነት፡ዛሬም፡ይበልጡኑ፡እየጎለበተና፡እየተጠናከረ፡መጥቶ፡በየተሰለፉበት፡ውድድር፡መድረክ፡ሁሉ፡አልበገሬነታቸው፡ዓለምን፡የሚያስደንቅ፡እየሆነ፡መጥቷል።

ዛሬ፡የኢትዮጵያ፡እና፡የኬንያ፡አትሌቶች፡የማይሳተፉበት፡ውድድር፡ሁሉ፡አይደምቅም፡በስነምግባር፡የታነጹት፡የሃገራችን፡ልጆች፡አረንጓዴ፡ቢጫ፡ቀዩ፡ባንዲራችንን፡ከፍ፡በማድረግ፡በድህነት፡በጦርነት፡በረሃብ፡የምትታወቀውን፡የኢትዮጵያ፡ሰንደቅ፡ዓላማዋ፡ከሃያላን፡ሃገሮች፡በላይ፡እንዲውለበለብ፡እያደረጉ፡ናቸው።ይህ፡ጀግንነት፡ከምን፡የመጣ፡ነው፡?አመጋገባቸው፡ምንድን፡ነው፡?የልምምዳቸው፡ሁኔታ፡እንዴት፡ነው፡?የሚሉት፡ጥያቄዎች፡በብዙ፡የስፖርት፡ተመራማሪዎች፡እና፡ባለሙዎች፡ዘንድ፡መነሳት፡ከጀመረ፡ሰንብቷል።ግን፡ከመንፈሰ፡ጠንካራነታችንና፡ከጽኑ፡የሃገር፡ፍቅራችን፡በቀር፡ምንም፡ድብቅ፡ሚስጢር፡እንደሌለ፡በእርግጠኝነት፡ለመናገር፡እወዳለሁ።
ብዙ፡የሃገራችን፡ህዝብ፡የማያውቃቸው፡በዓለም፡ታላላቅ፡ውድድሮች፡ላይ፡በመሰለፍ፡ከፍተኛ፡ድል፡ያስመዘገቡ፡በርካታ፡አትሌቶች፡አሉን፡ዛሬ፡ግን፡የት፡ናቸው፡? አረንጓዴው፡ጎርፍ"፡"THE GREEN FLOOD" የደጋ፡በራሪዎቸች፡ የሰማይ፡ዳርቻ፡የማይበግራቸው፡እና፡የመሳሰሉትን፡ስም፡ ያገኘንበትን፡ከ1970ዎች፡አጋማሽ፡ጀምሮ፡እስከ፡1980ዎቹ፡አጋማሸ፡ድረስ፡ያሉትን፡ዓመታት፡ብቻ፡እንኻን፡ብንመለከት፡ሃገራችን፡የብዙ፡ጀግኖች፡ሃገር፡መሆኗን፡ቢያንስ፡እንገነዘባለን።ከዚያ፡ዛሬ፡የትና፡በምን፡ሁኔታ፡ይገኛሉ፡የሚሉትን፡ጥያቄዎችን፡ለመመለስ፡ይቀለናል።
የሃገራችን፡አትሌቶች፡አረንጓዴ፡ለብሰው፡ተከታትለው፡በመግባት፡ከአንድ፡እስከ፡ዘጠኝ፡በአዋቂ፡፡ከአንድ፡እስከ፡ስድስት፡በወጣቶች፡የአለውን፡ቦታ፡አላስቀምስ፡ያሉበት፡ወቅት፡ነበር፡The Greenflood የሚለውን፡ስም፡ያሰጣቸው።እነ፡ግርማ፡ወልደሃና፡ ሀይሉ፡ወልደጻዲቅ፡ ወልዴ፡ሮበሌ፡ ቶሎሳ፡ቆቱ፡ ተክሌ፡ፈንቴሳ፡ አብርሃም፡ታደሰ(ፉል) እሸቱ፡ቱራ፡ መሃመድ፡ከዲር፡ምሩጽ፡ይፍጠር፡ ብርሃኑ፡ግርማ፡ ከበደ፡ባልቻ፡ ደጀኔ፡በየነ(ሾላ)፡ ደረጀ፡ነዲ፡ ስዩም፡ንጋቱ፡ ካሳ፡ባልቻ፡ ወዳጆ፡ቡልቲ፡ በቀለ፡ደበሌ፡ ጫላ፡ኡርጌሳ፡ አዱኛ፡ለማ፡ ፍስሃ፡አበበ፡ ነጋሽ፡ሃብቴ፡ ዙርባቸው፡ገላው፡ አራርሳ፡ፉፋ፡ አንጋሶ፡ታልጋ፡እና፡ሌሎችም፡ይገኙበታል።
ከእነዚህ፡አትሌቶች፡ውስጥ፤አብዛኛዎቹ፡በኢንተርናሸናል፡ደረጃ፡ከፍተኛ፡እውቅና፡የነበራቸውና፡በመደጋገም፡ የዓለም፡እና፡ የዓህጉር፡ ሻምፒዮና፡ሜዳሊያዎችን፡የተሸለሙ፡ሲሆኑ፡በዚያ፡ወቅት፡ሃገራችን፡ትከተል፡በነበረው፡የሶሻሊዝም፡ስርዓት፡የተነሳ፡በ10000ሜትር፡በ5000ሜትር፡በ3000መሰናክል፡በማራቶን፡እንዲሁም፡በእርምጃ፡ውድድር፡ የኦሎምፒክ፡ሜዳሊያ፡ማስገኘት፡እየቻሉ፡በፖሎቲካ፡ምክንያት ፡የሎስአንጀለስንና፡የሴኡልን፡ኦሎምፒኮች፡ሳይሳተፉ፡ቀርተዋል።
በዚያን፡ወቅት፡ኢትዮጵያ፡በሶምሶማ፡ወይም፡በእርምጃ፡ውድድር፡በተለይ፡በአፍሪካ፡ሻምፒዬናዎች፡ለብዙ፡ዓመታት፡በተከታታይ፡ያሸንፉ፡የነበሩ፡በአውሮፓና፡በሌሎች፡አህጉራት፡ብዙ፡ድል፡የተቀዳጁት፡ ሁንዴ፡ጦሬ፡ ሸምሱ፡ሃሰን፡እንዲሁም፡ተተኪዎቹ፡በቀለ፡ሁንዴ፡እና፡ በድሩ፡ከፍተኛ፡ችሎታ፡የነበራቸው፡አትሌቶች፡ነበሩ።
ይህ፡እግዲህ፡ በደርግ፡ዘመነ፡አገዛዝ፡ነበረውን፡ሁኔታ፡የሚዳስስ፡ሲሆን፡ከዚያ፡በፊት፡የነበሩትን፡የኦሎምፒክ፡ተሳትፎ፡በሚለው፡ጽሁፍ፡ስማቸውን፡በመጠኑ፡ለመጥቀስ፡ሞክሬአለሁ፡በእነ፡አበበና፡በአረንጓዴ፡ጎርፍ፡መሃል፡ደግሞ፡ራሱን፡የቻለ፡የእነ፡ባሻ፡ፍቅሩ፡ደገፋ፡ ባሻ፤ውሂብ፡ማስረሻ፡ ሸብሩ፡ረጋሳ፡ሮበሌ፡ጉርሙ፡እና፡መሳሰሉት፡የሮጡበት፡ዘመን፡ነበር።
ከአበበ፡ቢቂላ፡በስተቀር፡ዋሚ፡ቢራቱና፡ባሻ፡ፈለቀን፡ማሞን፡ጨምሮ፡በአካል፡አግኝቼ፡የመነጋገር፡እድሉ፡ስላገኘሁ፡ደስ፡ይለኛል፡ድርሻቸውን፡ታሪክ፡ሰርተው፡ካለፉት፡ሌላ፡በህይወት፡ያሉት፡በምን፡ሁኔታ፡እንዳሉ፡ሳስብ፡በጣም፡አዝናለሁ።የኔ፡ማዘን፡ግን፡ኑሮአቸውን፡አይቀይርም። አዲሶቹ፡እና፡እኛ፡ብንተባበር፡ግን፡አሮጌዎቹ፡ይታደሳሉ፡የሚል፡እምነት  አለኝ ::


No comments: